ሰዎች መጥተው ይቅርታ ቢጠይቁአችሁ መልሳችሁ ምን ይሆን?
ሰዎችን ይቅር ብዬሃለሁ ማለትና መተው መታደል ነው። በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ እግዚአብሔር ይቅርታን እሚያስተምረኝ ዘመን ነበር እና የተለያዩ ሰዎችን ይቅርታ እንድጠይቅ ያስተምረኛል እናም አንድ ሰውን ይቅርታ መጠየቅ ነበረብኝ ስለዚህ ሄድኩ ሳገኘው ይቅርታ እንድታደርግልኝ ፈልጌ ነው ይቅርታ አልኩ። ያሰው በጣም ተናደደ የማይሆን የማይሆን ነገሮችን ተናገረ ጭራሽ ነገሩ የባሰ የሆነ መሰለ። በዚያን ወቅት እኔ ብዙም አልጨነቀኝም ነገሩን ተቀበለው አልተቀበለው ሳይሆን እኔ ሄጄ ይቅርታ ማለቴ ብቻ ነበር ግዴታ አድርጌ ያሰብኩት። ምንአልባት አሁን ቢሆን ለዛ ሰው የተለየ መራራትና ሃዘኔታ ግድ ማለት ይበዛልኝ ነበር።

ጊዜያት አለፉ በተለያየ ጊዜ ይቅርታ መጠየቅና ይቅር ማለት የህይወቴ ክፍል ሆኖ ቀረ ። ከሰው ጋር ስንኖር ሊያሳዝኑን ቢችሉ ይቅር ብሎ መተውን የመሰለ ልብን የሚያሳርፍ ነገር እንደሌለ አውቄያለሁ። የሁለችን አይኖች በተከፈቱና ይህን ማየት በቻልን። ከይቅርታ የሚበልጥ የነፃ መውጣት ሚስጥር የለም።
እናም ዛሬ ይህን የምፅፍበት ምክንያት መጣ የኔ የሆነሰው አሳዝኖኝ ነበርና ትንሽ ከፍቶኛል ታዲታ ያሰው ደውሎ ይቅርታ በቀደም አሳዘንኩሽ ማለት፡ የሚሰማው ጆሮዬ ንግግሩን በትክክል መስማቱን ማረጋገጥ ፈለኩኝ፡ ማመን ከበደኝ ፣ ቀልድ መሰለኝ እንደውም ነገሩ በሆነ ሰአት የተሰማኝ ህመም ተመለሰ ፡ ይህ ቀልድ ነው እውነት? አይምሮዮ በሰኮንዶች ውስጥ ብዙ አሰበ ። እየተነገረ ያለው የይቅርታ ቃል ይልቅ የደረሰብኝ ሃዘን ገዝፎ ለመውጣት ታገለኝ። የሆነብኝን ነገር መናገር ጀመርኩ ወዲያው ግን ተመለስኩ ይቅርታ በመተው እንጂ በደልን በመቁጠር አይፈታም። እሺ ይቅር ብያለሁ ተውኩ አልኩ።
ምን አልባት አንተ አንቺ ይህን ስታነቢ በፍፁም ይቅር አልልም ያልሽበት ጉዳይ ይኖር ይሆን? ያንን ሰው ወይንም ወቅት በሃሳብ ላይ ሲመጣ ህመም ይሰማል? ሃዘን፡ ንዴት ይፈራረቅ ይሆን? እንግዲያው መፍትሄው አንድ ነው ሌላ መድሃኒት የለውም ይቅርታ ይባላል።
ማቲዎስ 5:7
የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።
እናም ሰውን ይቅርታ መጠየቅ መታደል ነው አንድ አንዴ ነገሩ የባሰ ቢመስል እንክዋን መንፈስ ልብን እንዲጠግን ተስፋ አድርጎ ማለፍ ያስፈልጋል። አሁን ያሰው ያኔ ይቅርታ ስጠይቀው ለምን እንደተናደደብኝ ገብቶኛል ለዛ ሰው አብዝቼ መፀለይ ነበረብኝ በራሱ አቅም ይቅርታን ሊሰጥ አይችልም እና አልፈርድበትም። ምን አልባት ዳግም ባገኘው ያን ሰው ሰላም በዝቶለት እንዳይ እመናለሁ።
በህይወት ውስጥ እጅግ አስፈላጊ ነገር፡ ግን ለብዙዎች የሚከብድ ቢኖር ይቅርታ ነው። አምላክ እራሱ በአካል መጥቶ ማስተማር የተጠበቀበት ለዚሁ ይመስለኛል። እናንተስ ምን ትላላችሁ ይቅርታ ጠይቃችሁ አለያ ተጠይቃችሁ ታውቁ ይሆን



